Teshome Girma Real Estate · Addis Ababa Book a consultation
← ወደ ማውጫው
Story 2 ደቂቃ Read in English

ከ1,000 በላይ ቤቶች እና 3 የማልደራደርባቸው መርሆች

በሪል ስቴት ዘርፉ ውስጥ ከ1,000 በላይ ቤቶችን እንዴት ሸጥክ ብላችሁ ብትጠይቁኝ… መልሴ አንድ አይደለም፤ ልክ እንደ ቤቶቹ ሁሉ ሺህ ነው። ግን ከሁሉም በስተጀርባ ሶስት መርሆች አሉ።

በሪል ስቴት ዘርፉ ውስጥ ከ1,000 በላይ ቤቶችን እንዴት ሸጥክ ብላችሁ ብትጠይቁኝ… መልሴ አንድ አይደለም፤ ልክ እንደ ቤቶቹ ሁሉ ሺህ ነው።

  • አንዳንዶቹን የሸጥኩት ደንበኛዬን በደንብ ስላዳመጥኩ ነው፤
  • አንዳንዶቹን ስላወራሁ ነው፤
  • አንዳንዶቹን እርምጃዬን ስላፈጠንኩ ነው፤
  • አንዳንዶቹን ደግሞ ቶሎ እርምጃ ከመውሰድ በመዘገየቴ ነው።

ይህንን ሁሉ ስኬት ግን እኔ ብቻዬን አላመጣሁትም። በ8 ዓመት የሪል ስቴት ጉዞዬ፣ ከሰርቬየርነት እስከ አመራር፣ ከቡድኔ ጋር በመሆን ውጤታማ የሆንነው በ3 የማልደራደርባቸው መርሆች በመመራታችን ነው።

1ኛ፡ እውነተኛ (Honest) መሆን

“እውነት እያደር ይጠራል” እንደሚባለው ውሸት መጋለጡ አይቀሬ ነው። በሪል ስቴት ውስጥ አንድ ውሸት አንድ ሽያጭ ሊያስገኝ ይችላል፤ ግን አንድ ደንበኛን፣ የእሱን ቤተሰብ እና የሚያውቃቸውን ሰዎች ሁሉ ለዘላለም ያሳጣል። እውነትን ይዞ የሚሰራ ሁልጊዜም ያሸንፋል፤ ዛሬ ባይሆን ነገ።

2ኛ፡ ከሽያጭ ይልቅ ደንበኛን ማስቀደም

የደንበኛን እውነተኛ ፍላጎት አውቃችሁ እሱን ለማገዝ መጣጣራችሁ፣ ዞሮ ዞሮ ሽያጩ በራሱ ጊዜ እንዲመጣ ያደርጋል። አንዳንዴ ይህ ማለት “ይህ ቤት ለእርስዎ ትክክለኛ አማራጭ አይደለም” ማለት ነው። የዚያን ቀን አንድ ሽያጭ ታጡ ይሆናል፤ ዘላቂ እምነት ግን ታተርፉበታላችሁ።

እምነት ከአንድ ሽያጭም በላይ ብዙ ርቀት ይዟችሁ ይሄዳል።

3ኛ፡ የቡድን አጋሮች ያለንን ግንኙነት ማጠናከር

አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናጠፋው አብረውን ከሚሰሩ ሰዎች ጋር ስለሆነ፣ ከእነሱ ጋር ያለን ግንኙነት አቅማችንን ሙሉ በሙሉ እንድናወጣ እና የሥራ አካባቢያችንን እንድንወደው ያደርገናል። 1,000 ቤቶች የአንድ ሰው ስራ አይደሉም፤ የአንድ ቡድን ስራ ናቸው።

ቤቶች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ

ገበያው ይለወጣል፤ ፕሮጀክቶች ይጀመራሉ፣ ይጠናቀቃሉ፤ ደንበኞች ይመጣሉ፣ ይሄዳሉ። እነዚህ ሶስት መርሆች ግን ከመጀመሪያው ቀን እስከ ዛሬ አብረውኝ ናቸው። ከ1,000 በላይ ቤቶች የሸጥኩበት “ምስጢር” ካለ፣ እሱ ይሄ ነው።

እናንተስ በስራም ሆነ በህይወታችሁ ላይ ከማትደራደሩባቸው መርሆች ምንድናቸው?

ውይይቱ LinkedIn ላይ ቀጥሏል

ሀሳብዎን በኮመንት ያካፍሉ

ጥያቄ አለዎት? የመጀመሪያው ንግግር ነፃ ነው — ሠላሳ ደቂቃ፣ በሚመችዎ ቋንቋ።

ቀጠሮ ይያዙ