Teshome Girma Real Estate · Addis Ababa Book a consultation
← ወደ ማውጫው
Global Insight 2 ደቂቃ Read in English

ቤታችሁ ያለፈቃዳችሁ ቢሸጥስ? የሲንጋፖር En Bloc ሽያጭ

በሲንጋፖር የአንድ ህንጻ ባለቤቶች በብዙኃን ድምጽ ህንጻውንና መሬቱን በጋራ ይሸጣሉ፤ ያልተስማሙትንም ጨምሮ። ቤት ስንገዛ በእርግጥ የምንገዛው ምንድን ነው?

ከአንድ ሪልስቴት ቤት ገዝታችሁ፣ ቤታችሁን አስውባችሁ፣ የተደላደለ ኑሮ እየኖራችሁ እያለ ድንገት አንድ ቀን… “ህንጻው እኮ ሊሸጥ ነው” የሚል ዜና ቢደርሳችሁ ምን ታደርጋላችሁ?

እናንተ “ቤቴን አልሸጥም፣ አልፈልግም” እያላችሁ ህንጻው ቢሸጥስ?

ይህ ነገር ኑሯችሁን ሲንጋፖር ውስጥ ካደረጋችሁ ሊፈጠር የሚችል “En Bloc” ወይም Collective Sale የሚባል ሂደት ነው።

ሂደቱ እንዴት ይሰራል?

En Bloc ማለት አንድ ህንጻ ላይ የሚኖሩ የቤት ባለቤቶች በጋራ ሆነው ህንፃውን እና ያለበትን መሬት ለአንድ አልሚ ወይም ኢንቨስተር ለመሸጥ የሚስማሙበት ሂደት ነው።

የሚገርማችሁ ነገር ደግሞ ይሄ ነው። እዚያ ህንጻ ላይ የሚኖሩ በቂ የቤት ባለቤቶች (በሲንጋፖር ህግ ለአሮጌ ህንጻዎች 80 በመቶ የሚሆኑት) በውሳኔው ከተስማሙ እና ሽያጩ ሁሉንም የህግ ሂደቶች ያሟላ ከሆነ፣ እናንተ ብትፈልጉም ባትፈልጉም ሽያጩ ሊቀጥል ይችላል።

ያልተስማሙትስ?

በስተመጨረሻ እናንተን ጨምሮ ሁሉም የቤት ባለቤት ከሽያጩ የሚገኘውን የራሱን ድርሻ ይቀበላል። አንዳንዴ እንደውም በግላችሁ ቤቱን ብትሸጡት ከምታተርፉት በላይ በጥሩ ዋጋ ቤታችሁ ሊሸጥ ይችላል፤ ምክንያቱም አልሚው የሚገዛው አንድ ቤት ሳይሆን ሙሉ መሬቱን ነው።

ኢንቨስተሩም ከእናንተ የገዛውን ህንጻ አፍርሶ በቦታው አዲስና ትልቅ ፕሮጀክት ሊገነባ ይችላል፤ ወይም መሬቱን ያዋጣኛል ብሎ ላሰበው ሌላ ዓላማ ያውለዋል።

አንድን ቤት ስንገዛ ያቺ የምንኖርባትን ጣሪያ እና ግድግዳ ብቻ አይደለም የምንገዛው። መሬት እንገዛለን፤ ቦታ እንገዛለን፤ ያ ቦታ ወደፊት ሊኖረው የሚችለውን ዕድልም እንገዛለን።

ለእኛ የሚሰጠው ትምህርት

በእኛ አገር እንዲህ አይነት ህግ የለም፤ ቤታችሁ ያለፈቃዳችሁ አይሸጥም። ነገር ግን የሲንጋፖር ልምድ የሚያስተምረን ትልቅ ነገር አለ፦ የቤት ዋጋ በግድግዳው ላይ ብቻ አይደለም፤ ከሥሩ ባለው መሬትና በዙሪያው ባለው ቦታ ላይ ነው።

ስለዚህ ቤት ስትገዙ “ይህ ቤት ዛሬ ምን ይመስላል?” ብቻ ሳይሆን “ይህ ቦታ ከ10 ወይም ከ20 ዓመት በኋላ ምን ይሆናል?” ብላችሁ ጠይቁ። ትክክለኛ ቦታ ላይ የተገዛ ቤት ጣሪያ ብቻ ሳይሆን ኢንቨስትመንትም ነው።

እናንተስ ከሌላ ሀገር የሰማችሁት ወይም ያያችሁት እና በጣም ያስገረማችሁ የሪል ስቴት እውነታ አለ?

ውይይቱ LinkedIn ላይ ቀጥሏል

ሀሳብዎን በኮመንት ያካፍሉ

ጥያቄ አለዎት? የመጀመሪያው ንግግር ነፃ ነው — ሠላሳ ደቂቃ፣ በሚመችዎ ቋንቋ።

ቀጠሮ ይያዙ