
ቤት ስትገዙ ቤቱን ብቻ አይደለም፤ ሰፈሩንም አብራችሁ ትገዛላችሁ
የሪል ስቴት ማስታወቂያዎች “መሐል… መሐል…” የሚለውን ቃል ደጋግመው የሚጠቀሙት ወደው አይደለም። የምትኖሩበት ቦታ የዕለት ተዕለት ኑሯችሁን ይወስናል።
የኢትዮጵያ የሪል ስቴት ማስታወቂያዎችን ስታዳምጡ አንድ ቃል ደጋግሞ ይሰማል፦ “መሐል… መሐል…”። ይህን የሚሉት ወደው እንዳይመስላችሁ። ቤት ስትገዙ ቤቱን ብቻ ሳይሆን ሰፈሩንም አብራችሁ እንደምትገዙት ስለሚረዱ ነው።
የምትኖሩበት ቦታ የዕለት ተዕለት አኗኗራችሁን፣ የስራ ህይወታችሁን፣ እንዲሁም ከቤተሰባችሁ ጋር የምታሳልፉትን ጊዜ እንኳን ሊወስን ይችላል።
ሰፈር ጊዜ ይሰጣል፤ ሰፈር ጊዜ ይወስዳል
እስቲ አስቡት። በየቀኑ 3 ሰዓት ትራፊክ ላይ የሚያሳልፍ ሰው እና በ10 ደቂቃ ወደ ስራው የሚደርስ ሰው በቀን ውስጥ የሚኖራቸው ጊዜ አንድ ነው? አይደለም።
በሳምንት ስናሰላው ልዩነቱ ወደ 15 ሰዓት ይጠጋል፤ በዓመት ወደ 700 ሰዓት። ይህ ጊዜ ከልጆች ጋር፣ ከጤና ጋር፣ ወይም ከሌላ ገቢ ጋር ሊውል የሚችል ጊዜ ነው። ስለዚህ የቤቱ ዋጋ የካሬ ሜትር ዋጋ ብቻ አይደለም፤ የጊዜ ዋጋም ጭምር ነው።
“መሐል ነው” ማለት ግን ፍፁም ነው ማለት አይደለም
መሃል ከተማ ላይ መኖር ለስራ፣ ለትምህርት፣ ለገበያ እና ለተለያዩ አገልግሎቶች ቅርብ ሊያደርጋችሁ ይችላል። ይህም የምታባክኑትን ጊዜ ይቀንሳል።
ነገር ግን መሐል መሆኑ ብቻውን መልስ አይደለም። የድምፅ ብክለት፣ የመኪና መጨናነቅ፣ የመናፈሻ ቦታ እጥረት እና ከፍተኛ የኑሮ ውድነት የመሳሰሉ ተግዳሮቶች ሊኖሩት ይችላል። ለአንድ ወጣት ባለሙያ ተስማሚ የሆነ ሰፈር፣ ልጆች ላሏት ቤተሰብ ላይመች ይችላል።
ከመወሰናችሁ በፊት እነዚህን ጠይቁ
ስለዚህ ቤት ስትገዙ “መሃል ነው?” ብላችሁ ብቻ አትወስኑ። ይልቁንም እነዚህን ጥያቄዎች ለራሳችሁ አቅርቡ፦
- ይህ ቦታ ለእኔ እና ለቤተሰቤ ተስማሚ ነው ወይ?
- መሐል መሆኔ በተጨባጭ ምን ይጠቅመኛል? ለስራዬ? ለልጆቼ ትምህርት ቤት? ለጤና አገልግሎት?
- የዚህ ሰፈር አኗኗር ከእኔ ጋር ይስማማል ወይ? ጸጥታ እፈልጋለሁ ወይስ ንቁ ከተማ?
- በተለያየ ሰዓት (ጠዋት፣ ምሽት፣ ቅዳሜና እሁድ) ሰፈሩን በአካል ጎብኝቼዋለሁ ወይ?
ቤት የዓመታት ውሳኔ ነው። ህንፃው ይታደሳል፤ የቤት ዕቃ ይቀየራል፤ ሰፈሩ ግን አብሯችሁ ይኖራል። ስለዚህ ቤቱን ከመመልከታችሁ በፊት ሰፈሩን ተመልከቱ።
ጥያቄ አለዎት? የመጀመሪያው ንግግር ነፃ ነው — ሠላሳ ደቂቃ፣ በሚመችዎ ቋንቋ።
ቀጠሮ ይያዙ