Teshome Girma Real Estate · Addis Ababa Book a consultation
← ወደ ማውጫው
Global Insight 3 ደቂቃ Read in English

አልሚዎች የዛሬውን ከተማ አይገዙም፤ የነገውን ነው የሚገዙት።

የሪል ስቴት አልሚዎችን ትርፋማ ከሚያደርጋቸው ጸጥ ያሉ ምስጢሮች አንዱ፦ አንድን መሬት ሲያዩ ዛሬ የከበበውን ሳይሆን ከአስር ዓመት በኋላ የሚከበውን ማየታቸው ነው።

ዛሬ ሚስጥር ላወጣ ነው! ብልሃት እንጂ ተንኮል አይደለም። የሪል ስቴት አልሚዎችን ትርፋማ ከሚያደርጋቸው ነገሮች ውስጥ አንዱን ልንገራችሁ — እና ይህ ነገር ከግንባታው ጋር ብዙም ግንኙነት የለውም። ከመቼ እና ከየት ጋር ነው ግንኙነቱ።

የቤት ዋጋ የግንባታው ወጪ ብቻ አይደለም

እንደ አዲስ አበባ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ላይ የቤት ዋጋን የሚጨምረው የግንባታው ወጪ ብቻ አይደለም። አንዳንድ ጊዜ ዋጋውን የሚጨምረው ቤቱ ሳይሆን፣ ቤቱ ያለበት አካባቢ ነው — በትክክል ለመናገር፣ ከተማዋ በዚያ አካባቢ ዙሪያ ልትሠራ ያሰበችው ነገር ነው።

ሁለት አፓርትመንቶች በአንድ ተቋራጭ፣ በአንድ ደረጃ፣ በአንድ ወጪ ሊገነቡ ይችላሉ። ከአምስት ዓመት በኋላ አንደኛው ከሌላኛው በእጅጉ ይበልጣል። ልዩነቱ በግንባታው ውስጥ አልነበረም። ልዩነቱ ከጎናቸው በመጣው ነገር ውስጥ ነበር።

አልሚው በትክክል የሚያየው ምንድን ነው?

አንድ ልምድ ያለው አልሚ ግንባታ መጀመር ሲያስብ መጀመሪያ የሚያየው የዛሬውን ከተማ ብቻ አይደለም። የተለየ ጥያቄዎችን ይጠይቃል፦

  • ይህ ቦታ ከአምስት ወይም ከአስር ዓመት በኋላ ምን ይመስላል?
  • እንደ ኮሪደር ልማት ያሉ አዳዲስ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ይሰሩበታል ወይ?
  • አዲስ የንግድ ማዕከል፣ የቢሮ ሕንፃ ወይም የአስፋልት መንገድ ይገነባበታል ወይ?
  • የከተማዋ ቀጣይ የእድገት ፕላን ወደየት ነው የሚያመለክተው — ይህ ቦታ በመንገዱ ላይ ነው ወይ?

ከዚያም ብዙ ሰው ትዕግስት የሌለውን ነገር ያደርጋል። አሁን ላይ የሰው እይታ ውስጥ ያልገቡ፣ መሰረተ ልማት ያልተሟላላቸው፣ መንገዳቸው ገና ጠጠር የሆነ፣ ሰፈር የማይመስሉ አካባቢዎች ላይ መሬቶችን አስቀድሞ ይይዛል።

አልሚው መሬቱን አሁን ባለበት ሁኔታ አይደለም የሚገዛው። ወደፊት በሚሆነው ሁኔታ ነው የሚገዛው።

ከዚያ ከተማዋ ትደርስበታለች

ልክ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እየተስፋፉ እና አካባቢው ተፈላጊነቱ እየጨመረ ሲመጣ፣ የቦታው ዋጋ ይጨምራል — ምናልባትም በእጥፍ። መንገዱ ከመድረሱ በፊት የገዛው አልሚ፣ መንገዱ ከደረሰ በኋላ ሁሉም ሰው የሚከፍለውን ትርፍ ያገኛል። ይህ ዕድል አይደለም። አርቆ ማየት ነው። የዛሬን ብቻ ሳይሆን የነገን አርቆ ማየት — ይህ ከአልሚዎች ስኬት ጀርባ ካሉ ብልሃቶች አንዱ ነው።

ለእናንተ፣ ለገዢዎች ይህ ምን ማለት ነው?

እናንተ ፎቅ ላትገነቡ ትችላላችሁ። ግን ይኸው ብልሃት በአንድ ቤት ወይም በአንድ መሬት ደረጃም ይሠራል። ቤት ወይም መሬት መግዛት ስታስቡ ዛሬ ላይ ያለበትን ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ነገ ቦታው ሊኖረው የሚችለውን አቅም አርቃችሁ ተመልከቱ፦

  • የከተማዋ ማስተር ፕላን እድገቱን ወደየት አቅጣጫ እየገፋ ነው?
  • በአቅራቢያው በግንባታ ላይ ያለ ወይም የጸደቀ የመንገድ፣ የኮሪደር ወይም የትራንስፖርት ፕሮጀክት አለ?
  • በጎረቤት መሬቶች ላይ አሁን ምን እየተገነባ ነው — በማን?
  • ትምህርት ቤቶች፣ ክሊኒኮች፣ ገበያዎችና ቢሮዎች ወደዚህ አካባቢ እየመጡ ነው ወይስ እየራቁ?

አንድ ቅን ማስጠንቀቂያ — ከእኔ መስማት ይሻላል፦ ቃል የተገባ ፕሮጀክት ሁሉ በጊዜው አይደርስም፤ አንዳንዱም ጭራሽ አይመጣም። ማረጋገጥ በምትችሉት ነገር ላይ ግዙ — በጸደቀ ፕላን፣ በተጀመረ ሥራ፣ በዓይናችሁ በምታዩት መንገድ — «ይመጣል» በሚባል ወሬ ላይ አይደለም። አርቆ ማየት ብልሃት ነው። ማንም ሊያረጋግጥ ለማይችል ነገ ዛሬ መክፈል ግን ብልሃት አይደለም።

ይህን ጉዳይ በጥልቀት ለማየት በአዲስ አበባ የመሬት ዋጋን በትክክል የሚያንቀሳቅሰው ምንድን ነው እና ቤት ስትገዙ ሰፈሩንም ትገዛላችሁ የሚሉትን ጽሑፎቼን ተመልከቱ።

ታዲያ ጥያቄው

ለመጨረሻ ጊዜ አንድ ቤት ስታዩ፣ ቤቱን ነበር የምታዩት — ወይስ አካባቢው ከአስር ዓመት በኋላ የሚሆነውን? አልሚዎቹ ሁለተኛውን ነው የሚያዩት። እናንተም እዚያ ብታዩ ይጠቅማችኋል።

ጥያቄ አለዎት? የመጀመሪያው ንግግር ነፃ ነው — ሠላሳ ደቂቃ፣ በሚመችዎ ቋንቋ።

ቀጠሮ ይያዙ